Monday, March 3, 2014

የመንግስት ባለስልጣናት ከተመረጡ ጋዜጠኞች ጋር ሊነጋገሩ ነው

በታህሳስ 2006 መጨረሻ የኢትዮጵያ ፕሬስ እና የኢትዮጽያ ዜና አገልግሎት ድርጅቶች ያጠኑትና ሰባት የግል መጽሔቶች ላይ ያተኮረ ጥናት ይዘት ላይ የሚወያይና ከፍተኛ የመንግስት ባለልጣናት የሚገኙበት ለጋዜጠኞች የተዘጋጀ ስብሰባ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በአዳማ እንደሚካሄድ ምንጮች ጠቆሙ፡፡

የመንግስት ድጋፍ ያላቸው የጋዜጠኛ ማህበራት ከመንግስት የኮምኑኬሽን ጽ/ቤት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት በተነገረለት ስብሰባ ላይ ከ100 በላይ የመንግስትና በገዥው ፓርቲ ደጋፊነት የሚፈረጁ የግል ጋዜጦች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ላይ አወዛጋቢ የሆነውና በታህሳስ ወር 2006 መጨረሻ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ ይፋ የተደረገው የሰባት መጽሔቶች የአዝማሚያ ጥናት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎአል፡፡
የአዲስዘመን ጋዜጣ አሳታሚ የሆነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና እና በህግ በፈረሰ ስም እስካሁን የሚጠቀመውና በመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ስር አንድ መምሪያ ሆኖ የተዋቀረው የኢትዮጽያ ዜና አገልግሎት ድርጅት አጥንተነዋል ባሉት የአዝማሚያ ጥናት መሰረት አዲስ ጉዳይ ፣ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ዕንቁ እና ሊያ የተባሉ መጽሄቶች ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30/2006 ዕትሞቻቸው የፖለቲካ ስርኣቱን የሚያጨልሙ፣ የአመጽ ጥሪዎችን የሚያቀርቡ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያጥላሉ፣ ህገመንግስቱን የሚያዋድቁ፣ የመንግስት ባለስልጣናትን የሚያጥላሉ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታእና የመሳሰሉት  ዘገባዎችን ማቅረባቸውን አጥኚዎቹ ማረጋገጣቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ጥናት መንግስት በቀጥታ በፕሬሶቹ ላይ ለመውሰድ ያሰበው እርምጃን ሕጋዊነት ለማላበስ የተዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ ከፍተኛ ትችቶች ሲቀርቡበት ቆይቷል።
በዚህ ሳምንት ዓርብ እና ቅዳሜ በአዳማ ይካሄዳል የተባለው ስብሰባ ምናልባት ወደቀጣይ ሳምንት ሊራዘም እንደሚችል የጠቀሱት የመንግስት ምንጮች፣ እስካሁን ባለው መረጃ ስብሰባው በዚህ ሳምንት ይካሄዳል የሚል ነው፡፡
በስብሰባው ላይ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በፕሬሶቹ ላይ የተካሄደው ጥናት ትክክለኝነት ለጋዜጠኛው ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል
http://ethsat.com/amharic/

12 ሺ ቶን ቡና በተጭበርበረ ሰነድ ወደ ውጭ አገር መላኩ ታወቀ

የስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ በቡና አስተዳደር ላይ የሚታየውን ችግር አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ 12 ሺ ቶን ወይም  1 መቶ 20 ሺ  ኩንታል ቡና በተጭበረበረ ሰነድ ወደ ውጭ ተልኮ መሸጡን አመልክቷል። ኮሚሽኑ ቡናው በማን በኩል ተሰርቆ እንደተላከ እያጣራ መሆኑን የዘገበው ሪፖርተር፣ የሽያጩ ገንዘብም ወደ አገር ውስጥ አለመግባቱን ገልጿል።

ዛሬ ባለው የአለም የቡና የመሸጫ ዋጋ 120 ሺ ኩንታል ቡና ከ16 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጣል። ይህን ያክል ገንዘብ በአንድ ጊዜ በተጭበረበረ ሰነድ መዝረፍ የሚቻልባት አገር ሆናለች የሚለው ዘጋቢያችን፣ ድርጊቱ መንግስት አለ ወይ ያሰብላል ሲል ሃሳቡን አሰፍሯል።
አቶ መለስ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት 10 ሺ ኩንታል ቡና መጥፋቱ ይታወቃል። ስለዚሁ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ መንግስታቸው እያጣራ መሆኑን ተናግረው ነበር። ይሁን እንጅ የምርመራው ውጤት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የታወቀ ነገር የለም።
ዘጋቢያችን እንደሚለው ጸረ ሙስና ኮሚሽን እየመረመርኩ ነው ቢልም፣ የምርመራው ውጤት ታፍኖ ሊቀር የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የንግድ ሚኒስቴር ባለስልጣናትን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የታመቀው ሮሮ ፈንድቶ ዛሬ በሽሚሲ ሁከት ነግሷል ! (ከነብዩ ሲራክ)

* የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ሆይ ለወገኖቻችሁ ድረሱላቸው!

* ተጸወእኖ ፈጣሪዎችም እታድክሙን ፣ ሂዱና እየሆነ ያለውን ተመልከቱ!
ሰሞኑን ከጅዳው የሽሜሲ ጊዜያዊ የእስር ማቆያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለወራት በእስር ተንገላታን ሲሉ የመረረ ሮሯቸውን ገለጹልኝ ። ሮሯቸወ ሰሚ ማጣቱን አምርረው የገለጹልኝ ወገኖች ከእኔ አልፎ ተርፎ ለጀርመን ራዲዮ የዝግጅት ክፍል ሳይቀር ምሬት ሮሯቸውን ማስተላለፋቸውን ገልጸውልኛል።Nebiyu Sirak
ዛሬ ረፋድ ላይም በተንቀሳቃሽ ስልኬ ደውለው እጃችሁን ስጡ ተብለው በሰጡ እየደረሰባቸው ያለው መጉላላት በመክበዱ ወደ የሞት ሽረት አድርገው ቁርጡን ለማወቅ እንደሚገደዱና ይህንንም ” ለጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ሃላፊዎችና ለአለም ድምጻችን አሰማልን !” ሲሉ እያለቀሱ ሃሳባቸውን ሲያስረዱኝ መጭውን ለመገመት አዳጋች አልነበረም!
የግፉአኑ የአደራ ቃል አለብኝና ስልኬን እንደዘጋሁ ወደ ጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ወደ ተጠባባቂው ቆንስል ጀኔራል ሸሪፍ ከይሩ ደወልኩ ። ስልካቸው ይጠራል ግን አያነሱትም! ደጋግሜ ደወልኩ መልስ የለም … ተስፋ ሰንቄ ወደ ሌላኛዋ የቆንስል መስሪያ ቤቱ ሃላፊ ወደ ቆንስል ሙንትሃ ደወልኩበ። እርሳቸውም አያነሱም! ደጋገምኩት ፣ መልስ ግን የለም ! የሚያዝ የሚጨበጥ ማጣት እንዴት ያማል?
ከሰአታት በኋላ እኩለ ቀን ከዚያው ከሽሜሲ ተደውሎለወኝ ስልኩን ሳነሳው የሰው ጫጫታ ፣ እሪታ ፣ አኡኡታና የጥይት ድምጽ ሰማሁ … ደዋዩን ወንድም ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ ? አልኩት “መረረን ፣ ድረሱልን አልን ፣ የሚሰማን አጣን ፣ እስር ቤቱን ሰብረን ወጣን !” አለኝ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ መለሰልኝ … ከዚያን ሰአት ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰአት ከሽሜሲ የሚደርሰኝ መረጃ ደስ አይልም ! የቆንስል መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በአካባቢው የተገኙ ቢሆንም መፍትሄ ማምጣት ግን የቻሉ አይመስልም !
የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ሆይ ለመረጃ ቅርብ ሁኑ ! ወገንን ለመደገፍ ትጉ ! የወገኔን የወገናችሁን ክፉ ደግ መረጃ እንዳላቀብል ፣ አታስተላልፍ ከፖለቲካው ጋር እያገናኛችሁ ከመወንጀል እስከ ተራ አሉባልታ የምትሞጅሩኝ የምትሞግቱኝ ተሰሚነት ያላችሁ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ሆይ ! አታድክሙን ! ስሙኝ ? እነሆ እየሆነ ያለውን ሂዱና ተመልከቱ ! የምትቆረቆረቆሩት ለወገኖቻችሁ ከሆነ እነሆ ድረሱላቸው !
በቃ ! ሌላ ምን ይባላል ?
ነቢዩ ሲራክ
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11300/

የዋሽንግተንና የአዲስ አበባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተተቸ ነዉ

በሙስና በእምነት ማጉደል በማታለልና በአመለካከት የሚለዩን ዝም በማሰኘት ሐይልን የያዛችሁ በተሳሳተየታሪክ ገጽታ ላይ ነው ያላችሁትቡጢያቹን የምትፈቱ ከሆነ እጅ እንዘረጋላችሗለን” ያሉት ኦባማ አንባገነናዊቡጢያቸዉን ካልፈቱአንባገነናዉያን ጋር  እጃቸዉን ዘርግተዉ ሲጨባበጡ መታየታቸዉ ትዝብት ላይእየጣላቸዉ ነዉ!

ዋሽንግተን ዲሲ፤ የካቲት 24/2006 (ቢቢኤን የዩናይትድ እስቴትስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን ገደብየለሽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማመላከት ያደረጋቸዉን ጥናቶች ዋቢ በማድረግበየካቲት 20/2006 ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።መሰረቱን አርሊንግተን ቨርጂኒያ ያደረገዉ ፖለቲኮ የሚባለዉ ጋዜጣ/መጽሔት የኦባማ አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግስትን ከመሰሉ ለነጻነት ምቹ ካልሆኑ አገራት ጋር ያለዉ ምጸታዊ የዲፕሎማሲ ቁርኝትንም ይተቻል።
ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ጀምሮ የዩናይትድ እስቴትስ መንግስታት ዜጎቻቸዉን ከሚጨቁኑ አገራት ጋር ግንኙነት ለመመስረት እምብዛም እንደማይጥሩ ፖለቲኮ እየገለጸ፤ለሚዛናዊነቱ ተስፋ የተጣለበት የኦባማ ካቢኔ ከሌሎቹ የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዝዳንቶች  በባሰ መልኩ ለዜጎቻቸዉ ደህነነት ምቹ ካልሆኑ 25 አገራት ጋር ግንኙነት አለዉ ሲል የኦባማን የብሐራዊ ደህነነትና ጥበቃ አማካሪ የሆኑትን ሱዛን ራይስ ንግግርን በዋቢነት ያቀርባል። ራይስ “ግልፅ እንሁን አንዳንዴ እኛ አጥብቀን የምንይዛቸዉን ዉድ የሆኑ መብቶችን ከማያከብሩ መንግስታት ጋር የስራ ግንኙነት አለን” በማለት በባለፈዉ የነሐሴ ወር መናገራቸዉን ፖለቲኮ ይገልጻል።
ፖለቲኮ ለነጻነት የማይመቹ ብሎ ከጠራቸዉ 25 አገራት ዉስጥ ኢትዮጵያን በቁጥር 11 ላይ ያስቀመጠ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ይመሯታል የምትባለዋ ኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህጓን ፖለቲከኞችን፣አክቲቪስቶችን፣መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉ አካላትን ለማሰር እንደ ማህተም ትጠቀምበታለች ሲል ተጠያቂ ያደርጋል።ፖለቲኮ አክሎም የመለስ ዜናዊ አስተዳደር በ1999 ሶማሊያን በመዉረር እራሱን ለዩናይትድ እስቴትስ ግልጋሎት ማቅረቡንያስረዳል። ይህንንኑ አጋጣሚ በመጠቀም በአሜሪካ የሰለጠኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከብሔር ብሔረሰቦች የተነሱ አማጺያንን ለማስቆም የጦርነት ወንጀል መፈጸማቸዉ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ክስ ቢቀርብበትም  ዋሽንግተን አዲስ አበባን በዲፕሎማሲ “እቅፍ-እቅፍቅፍ” እያደረገች መቀጠሏን ገልጿል።
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን ይጥሳሉ ከሚባሉት ጭቋኝ አገራት ጎራ ብትመደብም ፤እንደ አዉሮፒኣይኑ ቀመር በ2008 ብቻ ከዩናይትድ እስቴትስ 969 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ ተቀብላለች!
በኢትዮጵያ ዉስጥ ቀጣይ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ግድያ፣እስር፣የሐይማኖትነጻነትን መነፈግ፣የፕሬስ ነጻነት መመንመን፣የመማርና ማስተማር ሒደት ነጻነት በመንግስት መዳፍ ዉስጥ መግባት፣የመደራጀት-የመሰባሰብ-ሐሳብን በነጻ የመግለጽ ሁለንተናዊ መብት፣ የፍርድ ቤት አሰራር መበላሽትና በስልጣን መባለግን በመተንተን የዩናይትድ እስቴትስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በየካቲት 20/2006 አመታዊ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል። የኦባማ አስተዳደር አካል የሆነዉ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳቃቂ የሆነ የመብት ረገጣ ኢትዮጵያ ዉስጥ መኖሩን እያወጀ የኦባማዉ ቤተ-መንግስት ኢትዮጵያን ከመሰሉ በአንባገነናዉያን ከሚመሩ አገራት ጋር “መለስ-ቀለስ” ማለቱ እያስተቸዉ ነው። የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱን የሚመሩት ጃን ኬሪ አገራቸዉ ከስህተት የጠራች አለመሆኗን ያስረዳሉ።
“ዛሬ ስለ ሌሎች አገራት ያለዉ ሪፖርት ይፋ ለማድረግ ብንመጣም፤ እዚሁ አገራችን ላይ እራሳችንን በከፍተኛ መልኩ ተጠያቂ እናደርጋለን! እንከን የለሽ አለመሆናችንን እናዉቃለን” ጃን ኬሪ።
ጃን ኬሪ መስሪያቤታቸዉ ይፋ ያደረገዉ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ዋሽንግተን ዲሲ ባሉ የመስሪያ ቤቱ አባላት ጥናት ብቻ የተዘጋጀ  ሳይሆን በእያንዱ አገራት ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ሲያስረዱ “በመላዉ አለም ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች በጥናት እንደዚሁም እነዚህን ጽሁፎችን በመጻፍ አክቲቪስቶችን በመቅረብ መንግስታትን በማናገር የኤንጂኦና የሚዲያ ሪፖርቶችን በመተንተን አያሌ ሰአታትን አባክነዋል”ሲሉም ገልጸዋል።
ኬሪ ለነጻነትና ለመብት በሚደረግ ጥረት ዉስጥ ግለሰባዊ ሚና የጎላ መሆኑን መሆኑንም ይገልፃሉ።ከተለያዩ አገራት የለዉጥ ተምሳሊት የሚሏቸዉን ግለሰቦችን ስም በማንሳት የኢትዮጲያዉን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሚናን አድንቀዋል  “እስክንድር ነጋ ሐሳብን በነጻ ስለመግለጽ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚጽፍ ነው” ብለዋል።
በሚያዚያ 4/2004 የፔን አሜሪካን ሽልማትን ያገኘዉ እስክንድር ነጋ አለም አቀፋዊ ትኩረትን ያገኘ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ፈጠራ ወንጅሎት ከመስከረም 3/2003 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
የዩናይትድ እስቴስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነጻነትን ከሚነጥቁ ጥቂቶች ጋር ሳይሆን ነጻነትን ከተነፈጉ ብዙሗን አጋር በመሆን አብሮ እንደሚቆም ኬሪ ቃላቸዉን እያደሱ ይናገራሉ “ዛሬ ቃላችንን በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን! ክብርን ከሚነፍጉ ጥቂቶች ጋር ሳይሆን ክብርን ከሚሹ ብዙሗን ጋር አብረን ለመቆም ዝግጁ መሆናችንንም ለመግለጽ እንወዳለን!”በማለት ቢያስረዱም መንግስታቸዉ ከጨቋኝ አንባገነናዊያን ጋር በሚያደርገዉ ዲፕሎማሲያዊ ቅርርብ ተጠያቂ እየሆነ ነው።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ብዙ ቃልኪዳን የገቡት በራክ ኦባማ ቃሊኪዳናቸዉ አለተፈጸመም። በተመሳሳይ መልኩ ያሁኑ የዉጭ ጉዳይ መስራያ ቤት ሐላፊ ጃን ኬሪም ሆኑ የቀድሞዋ ሒላሪ ክሊንተን ከአንባገነናዊያን ጋር ያለዉን ግንኙነት ሲያደረጁ እንጂ ሲያመነምኑ አልተስተዋለም በማለት  በርካታ ምሁራን፣ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች ወቀሳ ያቀርቡባቸዋል።
በጥር 12/2001 ቃለመሃላ የፈጸሙት ፕሬዝዳንት ኦባማ ሰላምና ክብርን ለሚሹ የአለማችን ዜጎች የርሳቸዉ መመረጥ ብስራት እንደሆነ አመላክተዉ ነበር። ከትላላቅ የአለማችን መዲናዎች ጀምሮ ወላጅ አባታቸዉ እስከመጡበት የኬኒያ መንደር የተስፋ ቃል ነበራቸዉ! እንዲም በማለት  ስሜትን በሚነካ መልኩ ተናግረዉ ነበር…
“ከትላልቆቹ መዲናዎች እስከ አባቴ የተወለደባት መንደር ዛሬ ለሚመለከቱን ህዝቦችና መንግስታት፤ አሁን አሜሪካ የእያንዳንዱ አገር የእያንዳንዱ ግለሰብ ወዳጅ ናት! ሰላምና ክብርን ለሚፈልጉ ሴቶችና ህጻናት ዳግም ለመምራት ዝግጁ ነን” ፕሬዝዳንት በራክ ኦባማ።
ኦባማ ምንጫቸዉ ለሆነችዋ አፍሪካ ፕሬዝዳንታዊ ሐይላቸዉን በመጠቅም ያበረከቱት አስተዋፅኦ አናሳ ነዉ።ፕሬዝዳንቱ ቃለመሃላቸዉን ሲፈጽሙ ስልጣንን በማጭበርበር-በሙስናና የሐሳብ ልዩነትን በማፈን በሚቆናጠጡ አንባገነናዉያን ላይ ጣታቸዉን ቢቀስሩም ከነዚህ ምቹ ያልሆኑ አሳፍሪ መንግስታት ጋር እርሳቸዉም ይሁን ካቢኔአቸዉ ዲፕሎማሲያዊ ገደብን አለማበጀቱ አጠያያቂ እየሆነ ነዉ።
በአሜሪካዋ መዲና በዋሽንግተን ዲሲ ጥር 12/ 2001 ቀዝቃዉ አየር በጭብጨባ እየሞቀ ብዙዎች እያለቀሱ ኦባማ ለአንባገነናዊያን መልእክት አስተላልፈዋል።
“በሙስና በእምነት ማጉደል በማታለልና በአመለካከት የሚለዩን ዝም በማሰኘት ሐይልን የያዛችሁ በተሳሳተ የታሪክ ገጽታ ላይ ነው ያላችሁት! ቡጢያቹን የምትፈቱ ከሆነ እጅ እንዘረጋላችሗለን” ያሉት ኦባማ አንባገነናዊ ቡጢያቸዉን ካልፈቱ አንባገነናዉያን ጋር  እጃቸዉን ዘርግተዉ ሲጨባበጡ መታየታቸዉ ትዝብት ላይ እየጣላቸዉ ነዉ።
ብዙ የተገቡ ቃልኪዳስኖች ተግባራዊ ሳይሆኑ በየካቲት 20/2006 ከዩናይትድ እስቴትስ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአመቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲታወጅ “ከነጻነት ፈላጊዎች ጋር እንቆማለን!” የሚል ቃልኪዳን ተገብቷል።የዩናይትድ እስቴትስ መንግስት ባወጣዉ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የኢትዮጵያን መንግስት “ጨቋኝ-አፋኝ-አሳሪ-ገዳይ-ኢዲሞክራሲያዊ” መሆኑን ይፋ አድርጓል። ፖለቲኮ ጋዜጣ/መጽሔት ይህ ሪፖርት በወጣበት ማግስት የኦባማ አስተዳደር ኢትዮጵያን ከመሰሉ ለዜጎቻቸዉ ምቹ ካልሆኑ አገራት ጋር ይወዳጃል ሲል ይተቻል።
የዲሞክራሲ ተምሳሊት ነን የሚሉ የምእራቡ አገራት ለአንባገነናዊያን ዲፖሎማሲያዊ ከለላ መስጠታቸው የጥቅም ትስስር ወይስ ምጸታዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ጨወታ? የሚለዉ ጥያቄ ቢነሳም …ትችቱእንደቀጠለ ነዉ።
ሳዲቅ አህመድ
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11303/

የአድዋ ድልና ትሩፋት ፈተናዎቹ

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ADWA4



በእርግጠኝነት ኢትዮጵያዊ ልብ ላለው ሰው ሁሉ ስለ አድዋ ድል ሲሰማና ሲያወራ ልቡ በኩራት ይሞላል መንፈሱ ይነቃቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብቻም አይደለም በየትኛውም ዓለም ያለ በቅኝ ግዛት ቀንበር ፍዳ ያየ የትኛውም የሰው ዘር ጭምርም እንጅ፡፡ ይህን አንጸባራቂ ድል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተሰልፎ ካስመዘገበ እነሆ ነገ የካቲት 23 ቀን 2006ዓ.ም 118 ዓመቱን ይይዛል፡፡ ይህንን ድል ለመቀዳጀት ፈተና የነበሩት ነገሮች ምን ምን ናቸው? ለመሆኑ ይህ ድል እንዴት ተገኘ ?  የዚህ ታላቅ ድል ትሩፋቶችስ ምን ምን ናቸው? የዚህ ድል ጠላቶች እነማን ናቸው? ይህ ድል እንዴት ይጠበቃል? ብዙ ቢባልለት ከማይበቃው ከአድዋ ድል እነዚህን ነጥቦች ብቻ ነጥለን ለማየት እንሞክራለን፡፡
ዐፄ ምኒልክ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው ፋሽስት ጣሊያን በዘመነ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ከነበረበት አልፎ የትግሬ ገዥ የነበሩትን ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ከእሳቸው ቀጥለው እንዲነግሡ በማሰብ ሊሞቱ በሚያቃትቱበት ወቅት ወራሸ ነው ለእኔ ያደረጋችሁትን ሁሉ ለእሱም አድርጉ በማለት ተናዘውላቸው የነበሩትን ራስ መንገሻን ድል አድርጎ ሠራዊታቸውን ከበተነ በኋላ አልፎ መላዋን ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት ወደ መሸገባቸው ቦታዎች ወደ አንባ አላጌ፣ መቀሌ እንዳሥላሴና አድዋ ከመዝመታቸው እነዚያን አኩሪ ድሎች ከማስመዝገባቸውና ታሪክ ከመሥራታቸው በፊት እነኝህን ድሎች እንዳንቀዳጃቸው የሚያደርጉ እጅግ ከባባድ ፈተናዎች ተጋርጠውብን ነበር፡፡ የአድዋን ድል በሌሎች ሀገራት ከተገኙት ድሎች ልዩ የሚያደርገውም ይሔው ነው፡፡ እነዚህ ፈጽሞ ሊታለፉ የማይቻሉ መሰናክሎችን ታልፎ የተገኘ ድል በመሆኑ፡፡
የአድዋን ድል ለመቀዳጀት አያስችሉ የነበሩት ፈተናዎች ምን ምን ናቸው፡- 
  1. የከብት እልቂት፡- ፋሺስት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ ሲያስቡ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካና እስያ በቀላል ግጭት ቅኝ ሀገር መያዝ እንደቻሉ ሁሉ በኢትዮጵያ ይህ መልካም እድል እንደማያጋጥማቸው ጠንቅቀው ዐውቀውት ነበር፡፡ በመሆኑም ጦርነት መግጠማቸው የማይቀር ከሆነ የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አቅም ለማዳከም የሚያስችል ስልት ነደፈ ከስልቶቹ አንዱም የሀገሪቱ ሀብት መሠረት የሆነውን ግብርናዋን ማሽመድመድ መጉዳት ነበር፡፡ ይህንን ሲያስቡ ግብርናዋን ለመጉዳት ማድረግ የሚችሉት ነገር ሆኖ ያገኙት የከብት ሀብቷን መጨረስ ነበር፡፡ ይህንን ለመፈጸም ሲባል ከህንድ ሀገር ሶስት የታመሙ ከብቶችን በምጽዋ በኩል አስገብተው ከደማቸው እየወጉ የኞቹን ደኅናዎቹን ከብቶች በመውጋት አጋቡባቸው  በሽታውም በአጭር ጊዜ ተዛምቶ ከኢትዮጵያም አልፎ አጠቃላይ የቀጠናውን ከብት ፈጀው፡፡ ውጤቱም ፋሽስቶቹ ከጠበቁት እጅግ የበዛ ሆኖ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ‹‹ክፉ ቀን›› በመባል የሚታወቀውን ረሀብና ችጋር አመጣ፡፡ የሚበላ ነገር ጠፍቶ ዋልካ አፈርና ሳር ቅጠሉ ሁሉ የተበላበት ዘመን ነበር፡፡ ሕዝቡ ደቀቀ አለቀ ሀገሪቱ ተሽመደመደች፡፡
  2. የስንቅና ትጥቅ (logistics) ዝግጅት እጅግ ውስንነት፡- ፋሽስት ጣሊያን በወቅቱ ኃያላን ከሚባሉ የአውሮፓ ሀገራት አንዱ ነበረ፡፡ እንደ ኃያልነቱም ከ20 ሺ በላይ ለሆነው ላሰለፈው ጦሩ ዘመናዊ መሣሪያ በነፍስ ወከፍ ከማስታጠቁም ባሻገር ሠራዊቱ በወጉ የተደራጀ ዘመናዊ የውትድርና ሥልጠና የወሰደ ባጠቃላይ ከበቂ በላይ የስንቅና ትጥቅ ዝግጅት የነበረው ነበር፡፡ በእኛ በኩል የነበረው ደግሞ ባጋጠመው የረሀብና አስከፊ ችጋር የደከመ ሠራዊት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የሆነ የስንቅና ትጥቅ አቅርቦች ችግር ነበረበት፡፡ በወቅቱም ሠራዊቱ ነፍሱን ለማቆየት በቀን እጅግ መጥኖ ከሚቀምሳት በየ አገልግሉ ቋጥሮ ከያዛት ጥቂት ዳቦቆሎ፣ የደረቀና የሻገተ ቂጣ፣ ቆሎና በሶ የመድኃኒት ያህል ጥቂት ጥቂት የሚቀምስ ሠራዊት ነበረ እንጅ የስንቅ አቅርቦቱን አስቦ በየ ዕለቱ አብስሎ የሚያቀርብለት አካል አልነበረም፡፡ ሰራዊትም ሲባል ሐበሻ እንዲያው በተፈጥሮው ተዋጊ በመሆኑ እንጅ ሊገጥመው እንደተዘጋጀው ጠላቱ ሠራዊት በወጉ የወሰደው የውትድርና ትምህርት ጨርሶ አልነበረም፡፡ የታጠቀው መሣሪያም ቆመህ ጠብቀኝ በሚባል የሚታወቁ ኋላ ቀር መሣሪያ ሆኖ ይሄንንም ቢሆን የያዙት ከሠራዊቱ እጅግ ጥቂቶቹ ነበሩ የተቀረው ግን የያዘው ጦርና ጋሻ ጎራዴ ነበር፡፡ ይሔም አይጠቅምም ማለት ሳይሆን በጦር በጎራዴና በጋሻ ውጊያ የሚደረግበት ዘመን አልፎ ከሩቁ ጠላትን መልቀም ማስቀረት የሚቻልባቸው ከመድፍ እስከ መትረየስ ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች የወጡበት ዘመን በመሆኑ ለሚደረገው ጦርነት የጦር የጎራዴ እና የጋሻ ጥቅምና አገልግሎት እጅግ በጣም ውስን ሆኖ ነበር፡፡ ጦርነት በጦር በጎራዴ ይደረግ የነበረበት ዘመን ለእኛ እጅግ የቀና የበጀና የሰለጠም ነበር፡፡
  3. የባንዶች ሚናና የጠላት የመከፋፈል ስልት፡- ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማዳከም ከተጠቀመበት ስልት adwaiሌላኛው ባላባቶችንና መሳፍንቱን እስከ ራሶች ድረስ እንዲከዱ በማድረግ ከጎኑ ማሰለፍ ነበር፡፡ ጥቂት የማይባሉትንም ማስካድ ችሎ ነበር ነገር ግን እነዚህ የከዱና ከነሠራዊታቸው በባንድነት የተሰለፉ መኳንንት የጠበቁትንና የፈለጉትን አቀባበልና መስተንግዶ እንዳላገኙና እንደማያገኙም ሲገባቸው የዐፄ ምኒልክ ይቅር ባይነት ዋስትና ሆኗቸው ብዙዎቹ ተመልሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነኝህ ከድተው የነበሩ ሹማምንት መመለሳቸው የእውነት ከልብ ነው ወይስ ለተልዕኮ? የሚለው ጉዳይ ለወገን ሠራዊት በወቅቱ እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄና እውነቱን ለመረዳት ከመቸውም አጋጣሚ በበለጠ አምላክነትን የሚያስመኝ፤ ሥጋት ጥርጣሬውም እረፍትና እንቅልፍ የሚነሳ አምኖ ለማሰለፍም ለመተውም ያስቸገረበት ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡
  4. የፋሽስት ጣሊያን ጦር መሽጎ ያለ መሆኑ፡- ጦርነት በሚደረግበት ወቅት ጦርነት ከሚያደርጉት ባላንጣ አካላት አንደኛው ምሽግ ይዞ የሚጠብቅ ከሆነ ጦርነቱ ለአጥቂው ወይም ምሽግ ላልያዘው ክፍል እጅግ ከባድና አስቸጋሪ የሚያስከፍለው ዋጋም ከመሽገው አካል ጋር ሲነጻጸር በጣም የሚበዛ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ እኛንም ያጋጠመን ይሄው ነበር በሶስቱም ቦታዎች የጠላት ጦር ምሽጉን በሚገባ ገንብቶ ከምሽግ ማዶም በባዶ እግሩ የሚጓዘውን አርበኛ ሠራዊት እንዲቆራርጥ በጠርሙስ ስብርባሪና በጦር ችካሎች ከዚያም በፈንጂ የታጠረ ምሽግ ውስጥ ሆኖ አድፍጦና መሽጎ ይጠብቅ የነበረ ጦር ከመሆኑ የተነሣ የጠላትን ጦር ከዚህ ምሽጉ ለማስወጣት ምን ያህል መሥዋዕትነት ሊጠይቅና ሊያስከፍል እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ እንኳንና ተመጣጣኝ ትጥቅ ሳይያዝ ቢያዝም እንኳ ሁኔታው እጅግ ከባድ ነው በዚህ ላይ የእኛ ጦር ዘመናዊ የውጊያ ስልት ካለመማሩ ጋር ተያይዞ ተኝቶ መሬት ላይ በመሳብ መተኮስን እንደ ነውርና ፈሪነት አድርጎ የሚቆትር በመሆኑ ደረቱን ሰጥቶ በከፍተኛ ድፍረትና ወኔ ይዋጋ የነበረ ጦር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሥዋዕትነቱን እጅግ የከበደ አድርጎት ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ከነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ከጦርነቱ በኋላ የደረሰብን የሟችና ቁስለኛ መጠን በጠላት ሠራዊት ከደረሰው እምብዛም የሚበልጥ አልነበረም፡፡
  5. የህክምና አገልግሎት ችግር፡- እንዲህ ዓይነት የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ወረርሽኝ ይከሰታል፡፡ ወረርሽኝ ሲከሰትም ለዚህ ጉዳይ ቀድሞ የተዘጋጀ ህክምና ከሌለ ከባድ ጥፋት አስከትሎ ያልፋል፡፡ የወገን ጦር ይሔንን አደጋ መከላከል የሚችልበት አቅምና ዝግጅት አልነበረም ሌላው ቀርቶ ቁስለኛን እንኳን ማከም የምንችልበት መድኃኒትና ባለሙያ አልነበረንም ሁሉም ለየራሱ ሐኪም ነበረ፡፡ አስተናግር ቅጠሉን ጨምቆ አዘጋጅቶ ይዞት የመጣውን ቁስሉ ላይ እያፈሰሰ እርስ በራሱ ለመተካከም ይሞክራል እንጅ ይሔንን ጉዳይ የሚከውን የህክምና ቡድን አልነበረም፡፡
እንግዲህ እነዚህና ሌሎች ሊታለፉ የማይችሉ እንደተራራ የገዛዘፉ ከባባድ ደንቀራዎችን ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት በሐበሻነት ጽናት እናት አባቶቻችን አልፈው ነው የአንባላጌውን፣ የመቀሌውን፣ በመጨረሻም የአድዋን ድል ለመቀዳጀት የቻሉት፡፡ የአድዋ ድል በሌሎች ዜጎች ዘንድም በከፍተኛ አድናቆት የሚደነቀው የሚከበረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡Adwa_banner
ለመሆኑ ይህ ድል እንዴት ሊገኝ ቻለ?፡- ለድሉ መገኘት ትልቁ ድርሻ የእግዚአብሔር ረድኤት ቢሆንም እግዚአብሔር ሲሠራ በምክንያት ወይም መሣሪያ የሚያደርገው ነገር መኖሩ አይቀርምና ለእናት አባቶቻችን ቁርጠኝነትን፣ ጽናትን፣ መጨከንን ሰጥቶ ከቶውንም የማይታለፉትን ፈተናና መከራን አስተናግዶም በእነሱም ደክሞ ደቆ የነበረ ሕዝብ ተሰባብሮ ተነሥቶ እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ድል ለማስመዝገብ በቃ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ድል ለማስመዝገብ ሐበሻ ሆኖ መገኘትን የግድ ይጠይቅ ነበር አደረግነውም፡፡ በመሆኑም “ነፃነት ወይም ሞት” “ባሪያ ሆኖ ከመኖር ነፃ ሆኖ መሞት” የሚለው የጨከነ መርሑ ከፊቱ የተደቀኑ ግዛዙፍ ፈተናዎችን መሰናክሎችን ከነ አካቴው ከግምት ውስጥ እንዳያስገባ አድርጎት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ጽናት በመዋጋቱ ድሉን ሊያገኝ ቻለ፡፡
የዚህ ታላቅና አንጸባራቂ ድል ትሩፋቶች ምን ምን ናቸው? ይህ ታላቅ ድል ከእኛም አልፎ ለመላው ዓለም ጭቁኖች በርካታ ትሩፋቶችን አበርክቷል ከእነዚህ በርካታ ትሩፋቶቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
1. የቀለም ልዩነትን መሠረት ያደረገው የብቃት ደረጃ ልዩነት አስተሳሰብን ፉርሽ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡  ከዚህ ድል አስቀድሞ ጥቁር ሲባል ሰብአዊ እሴት አልባ፣ ለባርነት የተፈጠረ፣ ሥልጣኔ የማይገባው አድርገው ያስቡት ነበር፡፡ ከዚህም አልፈው ተናጋሪ እንስሳ እያሉ ይገልጹት ነበር፡፡ ጥቁሮቹ እናት አባቶቻችን ግን ፈጽሞ ሊታለፉ የማይቻሉ ፈተናዎችን አልፈው ለክብራቸው ለነፃነታቸው፣ ለሉዓላዊነታቸው የማይችሉት ነገርም እንኳን ቢሆን አንችለውምና ምን እናድርግ ብለው ክብራቸውን፣ ነፃነታቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውን ለድርድር ሳያቀርቡ ለሰብአዊ ክብራቸውና ለማንነታቸው ታይቶ በማይታወቅ ቀናኢነት በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ ማንኛውም ዓይነት የሰው ዘር አደርገዋለሁ ብሎ ሊሞክረው ቀርቶ ሊያስበው በማይችለው ሁኔታ በግሩም ችሎታና የአጨራረስ ብቃት ከውኖ በማሳየቱ ጥቁር እንዲህ እንዲህ ነው እየተባለ ዝቅ ተደርጎ ይቆጠርና ይታይ የነበረው አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን የግዳቸውን እንዲያምኑ አድርጓል፡፡
2. የነፃነት ትግልን አነቃቅቷል ቀስቅሷል፡- ጥቁር አፍሪካዊያን ለአምስት ምእተ ዓመታት ያህል በግፈኛ ነጮች ሲሰበክላቸው የኖረውን የጥቁርን ተገዥነት ወይም ለአገልጋይነት መፈጠር አምኖ ተቀብሎ ሰጥ ለበጥ ብሎ የመገዛትን አስተሳሰብ አዳብሮ ወደ አውሮፓና አሜሪካ እየተጋዘ እየተሸጠ እየተለወጠ ይገዛ ያገለግል ነበር፡፡ ሐበሾቹ ጥቁሮች አድዋ ላይ ያበሩላቸው ፀሐይ ግን ይሄንን የጨለመ አስተሳሰብ ጠራርጎ በማጥፋቱ የነጻነት ትግልንና የነፃነት ታጋዮችን በየስፍራው በየአቅጣጫው እንዲቀጣጠል አድርጎ እነሆ ዛሬ ላይ ያን ሁሉ ግፍ በጥቁርነቱ ብቻ ይጋት የነበረው የሰው ዘር ነጻነቱን አረጋግጦ ቢያንስ በገዛ ሀገሩ እንኳን እንደ ሰው መኖር የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንዲችል አብቅቷል፡፡Adwa__2
3. የተረሳውን ታሪካችንን አስታውሷል፡- ሐበሻ እንደሕዝብና እንደ ሀገር ከማንም የቀደመ የሥልጣኔና የመንግሥት ታሪክ ያለውና የነበረው ሕዝብ ነው ይህ ግን በወቅቱ በነበረው አስገዳጅ ችግር ሳቢያ ከዐፄ ፋሲል ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ቆይቶ በነበረው ዝግ መመሪያ (closed policy) ምክንያት ዓለም እኛን እኛም ዓለምን ረስተን ተረሳስተን ስለነበረ ዓለም በየጊዜው መረጃውን እያደሰ እንዳወቀን እዲቀጥል ማድረግ ሳንችል ቀርተን ነበር፡፡ የአድዋ ድል ግን ዓለም ስለኛ ያለውን መረጃ ካጎረበት እያወጣ እንዲያወራ እንዲህ እኮናቸው እንዲህእኮ ነበሩ እያለ እንዲያወራ አድርጎታል፡፡ ያወሩልን ይፅፉልን ከነበረው ታሪኮቻችን የሚበዛው እኛም እንኳን እራሳችን የማናውቃቸው ናቸው፡፡
4. የሕዝባችንን አንድነት አጽንቷል፡- የጠላት ወረራ ለመኳንንቶቻችንና ለመሳፍንቶቻችን ትልቅ ትምህርትን ሰጥቷል፡፡ በአንድነት የመቆምን አስፈላጊነት የአንድነትን ጥቅም በሚገባ አስገንዝቧቸዋል፡፡ ከዚያ አስቀድሞ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በመሳፍንቱና በባላባቶች ዘንድ የየራሳቸውን ጎጥ እንደ ሀገር በመቁጠር የየራሳቸውን ‹‹ሀገር›› የመመሥረት የማይጠቅምና ኋላ ቀር አስተሳሰብ ያስቡ ነበር፡፡ ይህን የትም የማያደርስ አስተሳሰብ ለማጥፋት ዐፄ ቴዎድሮስን እጅግ አድክሟል፡፡ በዐፄ ቴዎድሮስ እጅ ያደጉት ዐፄ ምኒልክ 2ኛም የዐፄ ቴዎድሮስ 2ኛ ሕልም ገብቷቸው ስለነበር ጥረታቸውና ሁኔታዎች ፈቅደውላቸው የዐፄ  ቴዎድሮስን ሕልም ለማሳካት ችለዋል፡፡ የአድዋ ድልም ለመሳፍንቱ የማይረሳ ትምህርትን ስለጣለላቸው ከዚያ በኋላ አስቀድሞ የነበረው ዓይነት የመሳፍንት አስተሳሰብ እንዳይኖር አድርጓል፡፡
5. ለቀጣይ ትውልድ ታሪክ እንዴት እንደሚሠራና እንደሚጠበቅ ምሳሌነቱን ትቶ አልፏል፡- ሀገራችን ከ4500ዓመታት በላይ የመንግሥት ታሪክ አላት እንደ ሀገር ከቆመችበት ጊዜ ጀምሮ ነጻነቷን ለመንጠቅ ተደጋጋሚና አደገኛ ፈተናዎችን አሳልፋለች፡፡ እነዚሁ ጣሊያኖች በቀደመው ስማቸው ሮማዊያን ከቄሳሮች ዘመን ከሁለት ሽህ ዓመታት በፊት ጀምረው ሲፈታተኑን ኖረዋል፡፡ የአድዋ ድል እናት አባቶቻችን የዚህችን ሀገር ነጻነት እንደምን ባለ መሥዋዕትነት አስጠብቀው እንደቆዩና ይህ ረጅም ታሪኳ እንዴት እንደተሠራ የቅርብ ጊዜ ምሳሌነት የተወ ድል  ነው፡፡ በደካማ ጎን መግባት የሚችሉበት ጠላቶቻችን ግን የትግል ስልታቸውን በቀጥታ ከሚተኮሰው አፈሙዝ ወደ ተለየ ዓይነት በመለወጥና ባንዶችን በማሠማራት የአድዋ ድል ከተወልን ምሳሌነት ልንማርና እኛም የድርሻችንን ታሪክ ልንሠራ የምንችልበትን ዕድል አጥበውት ሀገርን፣ አንድነትን፣ታሪክን፣ ነጻነትን፣ ሉዓላዊነትን፣ ክብርን መሠረቱ ያላደረገ የየግል ዓላማና አስተሳሰብ አራጋቢዎች አድርገውን አንድነታችንን አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡በዚህ ረገድ እየተሳካላቸው ይገኛል፡፡ ፈጣሪ ይቅደምልን እንጂ የዚህ ውጤት ደስ የሚያሰኝ አይሆንም፡፡
6. የታሪክ ሀብትን ትቶልናል፡- አንዲት ሀገር ዜጎቿ ጠንካሮች ከሆኑ ሁለቱም ሀብቶች ይኖሯታል ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች ታሪክ መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ ታሪክ መነቃቃትን የሚፈጥር ታላቅ ኃይል ነው፡፡ ቁሳዊ ሀብትም የመፍጠር ዐቅም አለው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለቱም ሀብቶች ነበሯት፡፡ ነበሯት ማለቱ ግድ ሆኗል አሁን ላይ ቁሳዊው እንደሌለ ግልጽ  ቢሆንም መንፈሳዊው ሀብታችንም ራሱ ድራሹ እንዲጠፋ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራበት ነውና ነበረን ማለቱ ይቀላል፡፡ ሊገባኝ ያልቻለው ነገር ግን ከዚህ ማን ምን ዓይነት ትርፍ አንዴት ሆኖ እንደሚያገኝ፤ ጥቅሙ ምን እንደሆነ ነው፡፡ ለሕዝቡ ልጠይቅ የምሻው አንድ ጥያቄ  አለኝ  የእናት አባቶቻችን ሀገር ኢትዮጵያ በዓለም  ውስጥ ከነበሩት አራት  ኃያላን መንግሥታት አንደኛዋ  ነበረች፡፡  ይህች ሀገር ዛሬ የዓለም  ጭራ ደሀዋ ሀገር ሆናለች ለምን? ይህ እንዴት ሲሆን ቻለ? እነሱ ጋር የነበረው ጠንካራ ጎን ይህችን ደሀና ደካማዋን ኢትዮጵያ ከፈጠርነው ከእኛ ጋር ያለው ደካማ ጎን ምንድን ነው?
7. ዕውቅናና መከበርን አትርፎልናል፡- ይህ ድል የማያውቁን አንዲያውቁንና ሀገር ለሀገር ለሚደረግ ግንኙነት ተመራጭ እንድንሆን አድርጓል፡፡ የሚያውቁንም እንዲያከብሩን አድርጓል፡፡ ባጠቃላይ ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ጠላትም እንዲሁ በተመሳሳይ ሳይወድ በግድ ዕውቅናና ክብር እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡ የዛሬን አያርገውና ከዚያ በኋላ ለመጣችው ኢትዮጵያም ሞገስን አጎናጽፎ በዲንሎማሲው (በአቅንዖተ ግንኙነቱ) ተደማጭ ተከባሪ እንድንሆን አድርጓል፡፡
8. ለመሪነት ሚና ተመራጭ እንድንሆን አድርጓል፡- ይህ ድል በሰጠን ዕውቅና ሳቢያ በተለያየ አቅጣጫ የፈጠራቸው በቅጭ ግዛት ይማቅቁ የነበሩ ሀገራት የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ይህንን እንቅስቃሴያቸውንና ትግላቸውን እንድንደግፍ እንድናስተባብር ለመጠየቅ አስገድዷቸዋል፡፡ ሀገራችንም ይህንን ትግል የመምራቱን ታሪካዊ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ በማመን ሀገራቱ ነጻ እስኪወጡ ድረስ የራሷን የጦር መሪዎችንና ተዋጊዎችን በማሰለፍ ጭምር ትግሉን ስታግዝ ስታስተባብር የተጣለባትንም አደራ በሚገባ ተወጥታለች፡፡ ለቀድሞው የአ.አ.ድ ለአሁኑ አ.ህ እና ለሌሎች አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫነት እንድትመረጥ ያበቃትም የዚሁ ድል ትሩፋት ነው፡፡
9. ሰንደቅ ዓላማችንን እንድንወስን አብቅቷል፡- በእርግጥ ከአድዋ ድል አስቀድሞም የሀገራችን ነገሥታት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ወይም አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአዋጅና በይፍ ዕውቅና ተሰጥቶት ሀገራችንንና ሕዝባችንን እንድትወክል  የተደረገው ዐፄ ሚኒልክ አድዋ ላይ ይህንን አንጸባራቂ ድል ከገኙ በኋላ እዚያው አድዋ ላይ  አዋጅ አስነግረው ከእንግዲህ ወዲህ ይህ ቀይ ቢጫ አረንጓዴ  ሰንደቅ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ  ሆኗልና ከክብር በላይ ክብርን፣ ከፍቅር በላይ ፍቅርን፣ ከአለኝታነት በላይ አለኝታነትን ስጧት ብለው በማስነገራቸው ይፋዊ ሰንደቃችን ሆና ለመቀጠል ቻለች፡፡Adwa_victory
   እንግዲህ በአጭር እንቋጨው እንጅ የአድዋን ትሩፋት እንዲህ በቀላሉ ዘርዝሮ የሚጨረስ   ጉዳይ አይደለም፡፡ በመቀጠል የአድዋ ድል ጠላቶች እነማን ናቸው? የሚለውንና ይህንን ቅርስ እንዴት ልንጠብቀው እንችላለን? የሚለውን በአጭር በአጭሩ ዐይተን እንቋጭ ፡፡
የአድዋ ድል ጠላቶች እነማን ናቸው?
 የእድለቢስነት ጉዳይ ሆኖ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለጠላት የታደለች ሀገር ነች፡፡ በዚህች ሀገር በየትኛውም ሀገር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለቁጥር የሚያታክቱ ጦርነቶች ከውጭና  ከውስጥ በሚፈጠር ቀውስ ሰበብ አስተናግዳለች፡፡ ይህች ሀገር ካስተናገደችው የጦርነቶች ብዛት አንጻር በታሪኳ በአማካኝ ከ10 ዓመታት ያለፈ የሰላምና የእፎይታ ቆይታ ዓይታ አታውቅም፡፡ ተአምር የሚሆንብኝ ነገር ቢኖር ይህንን ያህል የአውዳሚ ጦርነት ዓይነት ያስተናገደች ሀገር ደብዛዋ አለመጥፋቱ የሥልጣኔና የታሪክ አሻራዎቿም ጥቂቱንም ያህል ቢሆን መቆየት   መቻላቸው ነው፡፡ አሁን ላይ አስቀድሞ የነበሩን ጠላቶቻችንም ሆኑ ሌሎች አዳዲስ ቢኖሩ ጥቃታቸውን እየፈጸሙብን ያለው እንደቀድሞው በወረራ ሳይሆን በመሀከላችን ልዩነቶች እንዲፈጠሩ በማድረግና እርስ በእርስ በማናቆር በማፋጀት ሆኗል፡፡ ይሄም ይዞላቸዋል፡፡ አርቀውና አስፍተው ማሰብ የማይችሉ ወገኖቻችን የሀገራችን የሕዝብ  ለሕዝብ ግንኙነት  ምንም እንኳን እንከን የለሽ ነበር ማለት ባይቻልም በየትኛውም የዓለም ክፍል ከነበረው እጅግ የተሻለው እንጅ ተመሳሳይ እንኳን እነዳልነበረ፤ በበቂ ምክንያትና አማራጭም በመታጣቱ ለሀገር አንድነትና ህልውና ሲባል አንዳንድ የማያስደስቱን ነገሮች መደረጋቸውን መገንዘብ ማስተዋል የተሳናቸው ደናቁርት ለእነኝህ ጠላቶቻችን መሣሪያ በመሆን የሀገራችንንና የሕዝባችንን ህልውና ገደል አፋፍ ላይ አድርሰውታል፡፡ ዛሬ ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ያሉ የባርነትና ጭቆና ቀማሽ የነጻነት ደጋፊና አቀንቃኞች የሚኮሩበትን የሚያከብሩትን የሚያደንቁትን  የአድዋን ድልና ያንን ድል ያስገኙልንን አርበኞች እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በጥላቻ የሚመለከቱ መጥፋት መረሳቱን የሚፈልጉ ለዚህም የሚሠሩ ዜጐች ለማየትና ለመስማት ደርሰናል፡፡ መፍትሔው ምንድን ነው ትላላቹ?
 ይሄንን ቅርስ እንዴት ልንጠብቀው  እንችላለን?
 ይሄንንና  ሌሎች ቅርሶቻችንን ሀብቶቻችንን ታሪኮቻችንን ልንጠብቃቸው  የምንችለው ለነዚህ  ሀብቶቻችን አንድ ዓይነት መግባባት ሲኖረን ሀብቶቹ በሚገባ የመጠበቅ እድል ይኖራቸዋል፡፡ አእምሮ ካለን እዚህ አንድ ዓይነት መግባባት ላይ ላንደርስ የምንችልበት እንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ ወደራሳችን ወደ ውስጣችን እንመልከት፡፡ እያደረግነው ያለውን ነገር ከመፈጸሙ በፊት የሚገኘውን ትርፍና ኪሳራ እንመዝን፡፡ እንዲህ እንድናደርግ  እንድንናቆር እንድንባላ የሚመክሩን የሚገፋፉን የሚደግፍን ሀገራት በታሪካቸው ከእኛ የከፋ  የእርስ በእርስ ሰብአዊ መብት ገፈፋ ዝጋብ (record)  ያለባቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ነገሥታቶቻቸው ሲያርፉ ጠባቂ እያሉ ሰዎችን ከነነፍሳቸው ግራና ቀኝ ይቀብሩ የነበሩ ናቸው፡፡ የሰው ልጆችን ከአራዊት ጋራ እያታገሉና እያስበሉ ለመዝናኛነት ይጠቀሙ የነበሩ ሀገራት ናቸው፡፡ ይህ ተሞክሮ በሀራችን ፈጽሞ ኖሮ አያውቅም፡፡ ዛሬ ላይ እነሱ እንኳን አንድ ዓይነት መግባባት ደርሰው በአንድነት   ቆመው ለሀገራችው ጥቅሞች በአንድ የተሰለፉ ሆነዋል፡፡ እነሱ ለዚህ የበቁ እንደነዚህ ያሉ ዘግናኝና ኢሰብአዊ ድርጊቶችንና አስተሳሰቦችን ዓይተን የማናውቀው እኛ ኢትዮጵያዊያን እንዴት አንድ ዓይነት መግባባት ላይ ለመድረስ ያቅተናል? ለሀገርና ለሕዝብ እስካሰብን ጊዜ ድረስ ፈጽሞ አያቅተንም፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ጠልተንና ንቀን ባንዳነትን ከመረጥን ግን መቸም ጊዜ ቢሆን ልንግባባና የሰላም አየር ልንተነፍስ አንችልም፡፡
http://www.goolgule.com/adwa-and-its-benefits/

Monday, February 3, 2014

ህወሓት ከመለስ ጋር አብሮ ተቀብሯል

ከነፃነከነፃነት አድማሱ

ይህ የያዝነው ወርሓ ለካቲት “የህወሓት ልደት የትግራይ ህዝብ ልደት ነው፣ ህወሓት ብቸኛ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ነው፣ የትግራይ ህዝብ ታሪክ ከደደቢት ይጀምራል፣ የህወሓት አላማና ፍላጎት የትግራይ ህዝብ አላማና ፍላጎት ነው፣ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ሌላ አማራጭ የለውም ዙሪያው ሁሉ ገደል ወይም ጠላት ነው፣ በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ህልውና ከህወሓት ህልውና ጋር የተቆራኘና ድርጅቱ ስልጣን ላይ ሲኖር ትግራይም የምትኖር ድርጅቱ ከጠፋ ወይም ስልጣን ላይ ከሌለ ደግሞ የትግራይ ህዝብም አብሮ የሚጠፋ ነው”……..እያሉ በመስበክ በሰማእታት መቃብር ላይ ቆሞው የውሸት ድራማ የሚሰሩበት፣ በትግራይ ህዝብ ደምና አንጡራ ሃብት ላይ የሚነግዱበት፣ በድምሩ “ጆሮውን ቆርጠው የሰጡት ውሻ ሥጋ የሰጡት ይመስለዋል” እንዲሉ የትግራይ ህዝብ ብሄራዊ ክብሩ፣ ዳር ድንበሩንና ብሄራዊ ጥቅሙን ለባዕድ ሽጠው ሲያበቁ ነፃ አውጥተናሃል!! ልማት አምጥተንልሃል!! እያሉ የሚዘምሩበትና የሚመፃደቁበት የካቲት 11 በዓል እየመጣ ነው። ይህ ዓይነቱ ጭፍን ፕሮፓጋንዳ መርዝ ደግሞ ዛሬ የመጣ ባህል አይደለም። ህወሓት ከተፈጠረበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ ለአርባ ዓመታት ያህል ለጀሮ
እስከሚሰለች ድረስ በካድሬዎቹ አማካይነት ነጋ ጠባ በዚያች በተቀደሰች ምድር ትግራይ በአሁኑ በሃያ አንደኛ ክፍለ ዘመን የሚሰበክ የደደቢት የአደንቁረህ ግዛ ፍልስፍና መሆኑን ተራ የገጠር እረኛም ሳይቀር ያውቀዋል።Tigray People Front, TPLF
ይሁን እንጂ ህወሓት ከድርጅትነት ወደ ቡድናዊ አምባ ገነንነት፣ በኋላም ከቡድናዊ አገዛዝ ወደ ፍፁም የቤተሰባዊ መዝርፊያና የማፈኛ የግል ኩባንያ ሆኖ ከተሸጋገረ ወዲህ እኖሆ ዓሰርቱ ዓመታት አስቆጥሯል። በመጨረሻም “ጊዜ ዳኛ ታሪክ ምስክሩ ነውና” ድርጅቱ ከባለቤቱ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ጋር አብሮ ግብኣተ መሬት ገብቷል። ላይመለስ አብሮ ተቀብሯል። አሁን ያለው “በድርቆሽ የተሞላ ህይወት የሌለው የቆዳ ግሳንግስ ወደ(ዓርሲ)” ተለውጦ ባንድ በኩል በአቶ ስብሓት ነጋ የ80 ዓመት ጎበዝ አለቃ የሚመራ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኤርትራውያን የሚገፋ አሮጌ ጋሪና በወታደር የሚጠበቅ የደረቀ ሬሳ ሆኖ ቀርቷል” የሚሉ ብዙዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ይህ ምን ያህል እውነትነት አለው? አንድ የፓለቲካ ድርጅት ሞቷል ወይም ህይወት የለዉም ሲባልስ ምን ሲሆን ነው? ህወሓት ከበረሃ ጀግንነት ወደ ዱር አራዊትነት የተቀየረበት ጊዜስ መቼ ነው? እውነት የጥቂት ወሮ-በላና ከሃዲ መሪዎች በረሃ የገቡበትን ቀን የታላቁ የትግራይ ህዝብ ልደት ነውን? የትግራይ ህዝብ ከሌላው ሰማንያ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ምን የተለየ ጥቅም ስላገኘ ነው የአንድ መርሲነሪ የፓለቲካ ድርጅት ልደት የህዝቡን ብሄራዊ በዓል ተደርጎ የሚያከብረው? ለመሆኑ የትግላችን ውጤት ነው እየተባለ የሚነገርለት ሕገ መንግስት እውነት ለትግራይ ህዝብ ይመለከተዋልን? የሚሉና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎችን እንድንመልስ ግድ ይለናል።
ወደ ዋናው የጥያቄው መልስና አርእስተ ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ግን ለአንባቢዎቼና ለነፃ ሚዲያ ደንበኞቼ በአክብሮት የምጠይቀው በዚሁ ፅሑፍ ዙሪያ በመቃወምም ሆነ በመደገፍ ከቂም በቀል፣ ከስሜታዊ አስተሳሰብ፣ ከጭፍን ደጋፊነት፣ በአጠቃላይ የግለ ስብእና፣ የሃሳብ ነፃነትና
ሰብኣዊ መብት በማይጋፋ መልኩ በዋናው ጉዳይ ላይ ያተኰረ ክርክር ወይም ሃሳብ ቢያቀርቡ ለመማማርና በቂ መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆኔን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ። ፍርሃትን አስወግዶ የህሊና ባርነትን ሰብሮ በመውጣት የሀገርና የህዝብ ወገን ሆኖ መከራከር፣ ለሃቅ መመስከርና በፅናት መቆም ምንኛ ያኰራል!!!
በዘመነ መሳፍንት አንዲት የጎጃም አልቃሽ ““ጎጃሜ ቡዳ ነው ቡዳ ነው ስትሉ ስትሉ አላየህም ወይ ትግሬ እርስ በርስ ሲባሉ” ብላ ተናግራለች” በማለት ከዛሬ አስራ አንድ ዓመት በፊት የህወሓት አመራር ለሁለት ተሰንጥቆ ሲፈረካከስ ያዩ አንድ አዛውንት ያለፉትን የትግራይ ባላባቶችና መሳፍንቶች ታሪክ ከህወሓት ታሪክ ጋር በማነፃፀር እንደዋዛ አጫውተውኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በሌላ መልኩ ደግሞ ስለ ህዝቡ ጀግንነት፣ ጨዋነት፣ ታጋሽነትና አትንኩኝ ባይነት እያስታወሱ የዛሬው ትውልድ ግን ሐሙት የፈሰሰ እንዲሁ ወኔው ተኰላሽቶ መቅረቱ በጣም ያሳዘናቸው መሆኑን በቁጭት ገልፀውልኛል። ነገር ግን በወቅቱ የነገሩኝን ሁሉ ብዙም ልብ አላልኩትም ነበር። በኋላ ግን ስለ ህወሓት የተፃፉ መፃሕፍቶች በተለይም የቀድሞ የህወሓት ታጋይና አታጋይ የነበሩት አቶ አስገደ ገብረ ስላሴ የፃፉትን ጋህዲ በሚል ሶስት ተከታታይ መፃሕፍቶችን ሳነብ “ማየት ማመን ነውና” የትግሉ ባለቤትና የድርጅቱን መስራች የነበሩት ሰዎች እንኳን ሳይቀር የመሰከሩለት ህወሓት ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተግባሩ ሲመረመር ከላይ አዛውንቱ የነገሩኝ አባባል በትክክል የሚገልፅ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ።
“የህወሓት ታሪክ የርስ በርስ መላላት፣ ህዝብ ለህዝብ የማናቆርና ሀገርን የማፍረስ ታሪክ ነው” ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም። ይህን በሚመለከት ዝርዝሩን ለታሪክ ፃፊዎች ትቼ አንድ ሁለት አብነቶችን ብቻ ልጥቀስ። ህወሓት ከትጥቁ ትግል ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለ40 ዓመታት ያህል የዘለቀው አንድ ገዢ መፈክር ነበረው። እሱም “ የቻለ ይሩጥ!! ያልቻለ ያዝግም!! ያበቃለት ይለይለት!!? በትግርኛ (ዝኻኣለ ይጉየ! ዘይካኣለ ይሳለ! ዘብቀዐ ይታኣለ) የሚል ነው። ከመፈክሩም ጎን ለጎን በድርጅቱ የኪነት ቡድን የተሰራ ከአቶ መለስ መልክ ጋር የሚመሳሰል ፊት ለፊቱ ደግሞ ጣቱን ወደ ሰዎች ቀስሮ የሚያስፈራራ ሥዕል በየስብሰባውና ታጋዮች ባሉበት ሁሉ የሚለጠፍ ነበር።
ስዕሉ በጋሃድ በአደባባይ መውጣት የጀመረው ደግሞ ልክ እነ ዶ/ር አረጋዊ በርሄና አቶ ግደይ ዘርኣፅዮን ከድርጅቱ ተለይተው ከወጡ በኋላና “ማርክሰ ሌኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት)” ከተመሰረተ አንድ ዓመት ባልሞላ ውስጥ ነበር። ስዕሉ ያልተለመደ ነገር ስለነበረ ብዙ ታጋዮችን በተለይም ያልተማሩ የገበሬ ልጆች የሆኑትን ታጋዮች ግራ አጋብቷል። አንዳንድ ቦታም ሌሊት በሳንጃ እየቀደዱ ይጥሉት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ስዕሉ ተለመደ። የሚገርመው ግን በወቅቱ የድርጅቱን የኪነ ጥበብ አባል ሆኖ ስዕሉን ያቀነባበረ ሳኣሊውንም ጭምር ከጥቂት ወራት በኋላ ድርጅቱን ለቆ በመውጣት ዛሬ በስደት ዓለም በህወይት ይገኛል። ስሙን ያልጠቀስኩበት ምክንያት ደግሞ የሱ ፍቃደኝነት መጠየቅ ስላለብኝ ነው። የመፈክሩ ዋና አላማና ስትራተጂም የሚከተሉትን ሶስት ዋና ዋና ነገሮችን ያቀፈ ነው፡-
1. አንደኛ የአቶ መለስ ዜናዊና የአቶ ስብሓት ነጋ ቡድን ተቀናቃኝ ወይሞ ሞጎደኛ ተብለው የሚጠረጠሩትን ያመራር አባላት፣ ምሁራንና የጦሩ አለቆችን (ይህችን ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም) በማለት ቀስ በቀስ የማፅዳት ስልትና ስትራተጂ ነው። ይህንንም ሰሞኑን በኢትዮ- ሚዲያ ድሕረ ገፅ የወጣውን የነ ሙሴ፣ ዶ/ር አታክልት፣ ገሰሰው አየለን ጨምሮ ተኩሉ ሃዋዝ፣ መለስ ካሕሳይ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘርኣፅዮንና ሌሎች በሽዎች የሚቆጠሩት የድርጅቱን ከፍተኛና መካከለኛ የአመራር አባላትን ያካትታል።
2. ሁለተኛው የመፈክሩ አላማና ስትራተጂ የትግራይ ብሄረተኝነትንና ብሎም የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ከትግራይ ምድርና ከህዝቡ አስተሳሰብ ከስረ መሰረቱ በመፋቅና በማጥፋት በምትኩ በትግራይ ብሎም በሀገራችን የኤርትራ ሻዕቢያዊ አመለካከት የበላይነት እንዲይዝ ማረጋገጥ ነው። በዚሁ ዙሪያ በቅድሚያ የተመቱት የድሮ አስተሳሰብ፣ ሀገራዊ ስሜትና እንዲሁም በኤርትራ ጉዳይና በአገር አንድነት ጉዳይ ላይ የከረረ አመለካከት አላቸው ተብለው የሚገመቱትን ባላባቶችንና የሀገር አዛውንቶችን ናቸው። ቀጥሎም የተመቱት የትግራይ መሁራኖች ናቸው። በኤርትራና በሀገር ጉዳይ ዙሪያ የሚከራከሩና ጥያቄ የሚያነሱ ምሁራን እንደ ኤለክትሪክ ይፈሩዋቸው ነበር። በዚህ መሰረት “ሽዋውያን ተጋሩ” የሚል የቅፅል ስም መለጥፍ ብቻ ሳይሆን በዘፈንም ሳይቀር ቅስማቸው እንዲሰበርና አንገታቸው እንዲደፉ ተደርጓል። በዚህ ምክንያት የቻሉትን ከድርጅቱ ሸሽተው እንዲያመልጡ ያልቻሉት ደግሞ ለእስርና ለግድያ ተዳርጓል። በዚህ ምክንያት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ምሁራን ዛሬም ስለህዝባቸውና ሀገራቸው ጉዳይ ደፍረው ጥያቄ እንዳያነሱ ፍርሃት እንደ ወባ
በሽታ በደማቸው ውስጥ ገብቶ እያዩ እንዳላዩ ዝም እንዲሉ ትልቅ ምክንያት የሆነውን ጠባሳ እስካሁን ድረስ አልሻረም።
ዛሬ በአረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎቻቸው እየደረሰ ያለው ዱላም ከዚሁ የተለየ አይደለም። ለአንድ የአረና አባል ከአምስት በላይ ሰላዮች በመመደብ ኮቲያቸውን እየተከተሉ መውጫና መግቢያ ያሳጧቸዋል። ዛሬ ትግራይ ለነ ስብሓት ነጋና ሌሎች መሪዎች ታማኝ የሆኑትን የኤርትራ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶች በነፃነትና በልበ ሙሉነት የሚንቀሳቀሱባት በአንፃሩ ከህዝቡ አብራክ የተፈጠሩ ለነ አረና ትግራይና ሌሎች ሀገር በቀል ድርጅቶች ግን በገዛ ሀገራቸው ተሸማቅቀውና በአደባባይ በዱላ እየተመቱ የሚኖሩባት ምድራዊ ሲኦል ሆና ትገኛለች።
በመሆኑም ዛሬ ሰፊው የትግራይ ህዝብ ባንድ በኩል የትግራይ ሻዕቢያ በሌላ በኩል ደግሞ የኤርትራ ሻዕቢያ አጣብቅኝ ውስጥ ገብቶ በሁለት አለንጋ እየተገረፈ የሚገኝ ህዝብ ሆኗል። ታዲያ!! ለዘህ ሚስኪን ህዝብ አለሁልህ የሚል ወገን ማን ይሆን?
3. ሶስተኛው የመፈክሩ አላማና ስትራተጂ በህዝቡ የስነ ልቦናና የአካል ጥቃት በማድረስ በተለይም በትግራይ ምድር ፍርሃት፣ ሽብር፣ ጥርጣሬና ህወከት በማንገስና የህዝቡን ሁለንትናዊ አስተሳሰብ በመቆጣጠርና በማደንዘዝ ፀጥ ረጭ ብሎ እንዲገዛና ለጥቂት መሪዎች ዘላለማዊ ስልጣን አገልጋይ ሆኖ እንዲኖር ለማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር ትግራይ ወፍ እንኳን ዞር የማይልባት፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ በትግራይ ህዝብ ጉዳይ ላይ እንደማያገባው ተደርጎ መፈናፈኛ በማሳጣት በስመ ልማት እንደፈለጉ የሚግጥዋት የህወሓት የጓሮ አትክልት ሆና እንድትኖር ለማድረግ ነው።
ልበ በሉ!! የትግራይ ህዝብ በጦርነት የደቀቀ ህዝብ ነው። ትግራይ ደርግ፣ ኢዲዩ፣ ጀብሃ፣ ሻዕቢያ፣ ኢሕአፓ፣ ህወሓትና ሌሎች ብረት ያነገቡ ሀይሎች የሚንቀሳቀሱባት ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል የጦርነት አውድማ ሆና ቆይታለች። ዛሬም ህዝቡ ከጥይት ጭኾት አልተላቀቀም። በኤርትራና በኢትዮጵያ በሁለቱም ሀገሮች ድንበር ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሰራዊት በመሸገበትና በተፋጠጠበት የጦርነት ደመና ስር ሆኖ ዛሬ ነገ ውጊያ ይጀመራል እያለ በፍርሃት ተውጦ የሚገኝ ህዝብ ነው። በዚህም ላይ በየጊዜው ከያሉበት በታጣቂዎች እየታፈኑ ወደ ኤርትራ ተወስደው ደብዛቸው የማይታወቁ ንፁኃን ዜጎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በዚሁ ፍርሃት ቀያቸውንና ቤታቸውን እየለቀቁ ወደ ዓረብ ዓለም የሚሻገሩና ወደ ማሀል ሀገር በመሸሽ የኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞችን በልመና ያጥለቀለቁት የየተኛው አካባቢ እንደሆኑ ማንም ኢትዮጵያዊ ያውቃል። እነዚህ ግጭቶችም እንደ ፓለቲካ መሳሪያና ማስፈራሪያ እየተጠቀሙ “እኛ ከሌለን ያ ሁሉ
ጠላት ይመለሳል፣ ሻዕቢያ ተመልሶ ይውጥሃል፣ ኦነግና ትምክሕተኞች ቂማቸው ይወጡቡሃል፣ የሽብርተኞች ዒላማ ትሆናለህ፣ በትግራይ የተተከሉ ፋብሪካዎች ተነቅለው ወደ ማሃል ሀገር ይወሰዳሉ፣ በትግልህ የቀበርካቸው ጠላቶች ከመቃብር ተነስተው ይመጣሉ፣ ወዘተ እያሉ ነጋ ጠባ ህዝቡን ማሸበርና ማደንቆር የተካኑበት ዋነኛ የአገዛዝ ጥበባቸው ሆኖ ይገኛል።
ወንድሞቼ ሆይ!! ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ የቆሸሸ ታሪክ ያለው ድርጅት ዛሬ በትግራይ ህዝብና በተለይም በአረና አባላትና ደጋፊዎቻቸው ላይ የአራዊት ስራ ቢሰራ የሚያስገርም አይደለም። ህዝብን ሁሉ ጊዜ ማታለል የማይቻል መሆኑን ያልገባቸውና ጊዜውም ጥሏቸው እየሄደ መሆኑንም የማይቀበሉ እንደ ሾላ ፍሬ ውስጣቸው የበሰበሱ መሪዎች እስከ ህልፈተ ቀናቸው ድረስ “የደንቆ ልቅሶ መልሶ መላልሶ” እንዲሉ ዛሬም የሚናገሩት ቋንቋና የሚሰሩት ስራ ያው በጫካ የለመዱት ዓይነት ነው። ከላይ የተጠቀሰው የመፈክራቸው አላማና ስትራተጂም በትክክል ሲተረጎም “እምቢ ያለ ሰው ጥይት አጉርሰው” ከሚለው የደርግ ስርዓት መፈክርና ተግባር ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ይስቷል ብዬ አልገምትም።
የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ነገር ግን ትግራይን የጥፋትና የመከራ ሞዴል በማድረግ የሚፈፅሙትን ጉድ እንደ ኤይድስ ወረርሽኝ በሽታ ወደ ሌሎቹ ክፍላተ ሀገራትም እየተዛመተ መምጣቱ ነው። በዚሁ ነጥብ ዙሪያ በቀጣዩ ፅሑፌ ተመልሼ እመጣለሁ። ቸር ሰንብቱ።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10902/

ሳልቫ ኪር እና ሬክ ማቻር ለደቡብ ሱዳን ቀውስ ተጠያቂዎች ናቸው – ኦባንግ ሜቶ


obang metho1

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ የደቡብ ሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከኬኒያው ቴሌቪዥን KTN ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሳልቫ ኪር እና ሬክ ማቻርን ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በትጥቅ ትግሉ ወቅት በረሃ እንደነበሩበት ሁኔታ በነጻ አውጪ አእምሮ አገር መምራት የለባቸውም በማለት ወቅሰዋል፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያለ በዘር እና ጎሣ ላይ የተመሠረተ አገዛዝን ተግባራዊ ያደረገ ቡድን ለደቡብ ሱዳን የዘርና ጎሣ ችግር መፍትሔ ማምጣት አይችልም፤ በአገዛዝ ላይ ያሉት የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎችም ሆኑ የዑጋንዳውን መሪ በአምባገነንነት ከ20 ዓመታት በላይ በሥልጣን የቆዩ በመሆናቸው ለሳልቫ ኪር አምባገነናዊነትን ያስተማሩና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መሸምገል የሚችሉ አይደሉም ብለዋቸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ በኬኒያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ተገኝተዋል፡፡ (ውይይቱን ለማዳመጥ እዚህ ላይ ይጫኑ)
http://www.goolgule.com/obang-on-ktn/